26/04/2026
በአክሱም ከተማ አቅራቢያ የነበረው ታሪካዊው የዱራ መስጂድና የደረሰበት ጥቃት!
• ሀሩን ሚዲያ | ሚያዝያ 15 ቀን 2018 ዓ.ል
በጣሊያን ወረራ ወቅት የኢጣሊያ መንግስት የሙስሊሙን ማህበረሰብ ድጋፍ ለማግኘት ሲል ከአክሱም ከተማ በ3 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘውና ሙስሊሞች በብዛት በሚኖሩባት የዱራ ከተማ መስጂድ እንዲገነቡ ፈቃድ ሰጥቶ ነበር።
በዚህች አነስተኛ ከተማ በአንጻራዊነት ሙስሊሞች የሚበዙ ሲሆን፤ የጣሊያን መንግስት በሰጠው ፈቃድ መሠረት የዱራ መስጂድን ገንብተው የአምልኮ ተግባራቸውን መፈጸም ቻሉ።
በወቅቱ ሀገሪቱን ሲያስተዳድር የነበረው የአጼ ሀይለስላሴ ንጉሳዊ መንግስት ያልሰጣቸውን የአምልኮ ነጻነት መብት በጣሊያን መንግስት ያገኙት ሙስሊሞች፣ በአክሱም ከተማና አካባቢዋ አንጻራዊ ነጻነትንና የዜግነት እኩልነትን አገኙ።
በዚህ ጊዜ በአካባቢው መስጂድ መሰራቱን የተቃወሙና የሙስሊሞች የአምልኮት ነጻነት መከበሩን ያልፈለጉ አካላት፣ የዱራ መስጂድን በሌሊት በመምጣት ማፍረሳቸው ይነገራል።
በአክሱም ከተማና አካባቢዋ ሙስሊሙ ማህበረሰብ መስጂድ ቀርቶ የመኖርያ ቤትና መሬት እንዳይኖረው ሲተገበር የቆየው ስውር ስርዓት በሶሻሊስት መሩ የደርግ መንግስት ፖሊሲ ተገረሰሰ።
የደርግ ስርዓት የሀይማኖት እኩልነትን በማወጅ ሙስሊሞች በአክሱም የመኖርያ ቤትና የመስሪያ ቦታዎችን በእኩልነት እንደማንኛውም ዜጋ ሊያገኙ እንደሚገባ መመርያ በማውጣት፣ ሙስሊሞች በ30 ብር ክፍያ በአክሱም የመኖርያና የመስሪያ ቦታ እንዲመሩ ማስደረጉ ይገለጻል።
የአክሱም ሙስሊሞች በባዕድ ሀገር መንግስት የተሰጣቸው የአምልኮ ቤት በሌሊት መፍረሱን ተከትሎ፣ በ1990 ዓ.ል በወቅቱ ለነበረው ለኢህአዴግ መንግስት፣ ለወረዳው አስተዳደር፣ ለዞኑና ለክልሉ መንግስት መስጂዱን መልሶ ለመገንባት ጥያቄ አቀረቡ።
በተዋረድ ለሚገኙ የክልሉ መንግስት ቢሮዎች አቤቱታ ያቀረቡት የአክሱም ሙስሊሞች፤ ምንም እንኳን በቀድሞው የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ጸጋይ በርሄና የዞኑ አስተዳዳሪ ጽጌ በየነ መስጂዱ እንዲገነባ ደብዳቤ ቢጻፍም፣ በአካባቢው በሚገኙ ኢስላም ጠል አካላት ግንባታው እንዳይከናወን ተደረገ።
የአክሱም ከተማ ሙስሊሞች ለዘመናት የመስገጃና የመቀበርያ ቦታ ተከልክለው የቆዩ ሲሆን፤ ባሳለፍነው ሚያዝያ 2 ቀን 2018 ዓ.ል በግለሰቦች ቤት ተከራይተው የጁምዓ ሶላታቸውን በሚሰግዱበት ወቅት በጸጥታ አካላት ለድብደባና ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል። ለዚህ ጥቃት መነሻ የሆነውና ቀደም ሲል በንቡረ እድ ጎደፋ የተደረገው ቅስቀሳ ሲሆን፤ "እስከ ግንቦት 7 ድረስ በአክሱም 'አላሁ አክበር' የሚል ድምጽን መስማት ስለማንፈልግ የአክሱም ከንቲባ ያስቁምልን" የሚለው ቅስቀሳና ሂጃብ መከልከል አለበት የሚለው የንቡረ እድ እና መሰል የሀይማኖት አባቶች የጥላቻ ቅስቀሳ ለጥቃቱ መንስኤ መሆናቸው ተነግሯል።
የአክሱም ሙስሊሞች በጣሊያን ወረራ ወቅት የገነቡት የዱራ መስጂድ በኢስላም ጠል አካላት ከፈረሰ ከ30 ዓመታት በላይ የሆነው ሲሆን፤ የከተማዋ ሙስሊሞች ህገመንግስቱ የሚያስቀምጠውን የእምነት ነጻነት በመጣስ የመስጂድ፣ የመቃብርና የሂጃብ እገዳዎች አሁንም እንደቀጠሉ መሆኑ ተመላክቷል።
📅 ዙል-ቂዕዳ 6 ቀን 1447 ዓ.ሂ
© ሀሩን ሚዲያ