Belay tiguh

Belay tiguh church imformation

04/06/2022
25/05/2022

+ ቅዱስ ዶክተር ሉቃስ +

መጽሐፍ ቅዱስን እጅግ አስደናቂ መጽሐፍ ከሚያደርጉት ብዙ እውነታዎች አንዱ ሃሳቡ አንድ ሆኖ ሳለ የጸሐፊዎቹ ማንነት ግን እጅግ የተለያየ መሆኑ ነው፡፡ እረኞች ፣ ነገሥታት ፣ ዓሣ አጥማጆች ፣ ሰዓሊዎች ፣ የሂሳብ ባለሙያዎች ፣ ገበሬዎች ፣ ድንኳን ሰፊዎች ፣ ሐኪሞች በአጠቃላይ የተለያየ ሙያ ያላቸው ሰዎች ነበሩ - ጸሐፊዎቹ፡፡ ከእነዚህ ብዙ ጸሐፍት ውስጥ የሦስት ሙያዎች ባለቤት የሆነው ጠቢቡ ቅዱስ ሉቃስ ይገኝበታል፡፡ ይህ ወንጌላዊ በሙያው ጸሐፊ ፣ ሰዓሊ እና ሐኪም ነበረ፡፡

‹ባለ መድኃኒቱ ሉቃስ› በተጨማሪም በወንጌሉ ላይ ሐኪምነቱን የሚያስረዱ ብዙ አሻራዎችን አስቀምጧል፡፡ (ቆላ. 4፡14) የጸሐፊያንን ማንነት በጽሑፋቸው ውስጥ ፈልጎ ማግኘት የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት አንዱ ጥበብ ነው፡፡ ለምሳሌ የዕብራውያን መልእክትን ቅዱስ ጳውሎስ እንደጻፈው በመልእክቱ ላይ አልተናገረም ነበር፡፡ ይህንንም ያደረገው ዕብራውያን ለእርሱ ባላቸው ጥላቻ ምክንያት መጽሐፉን ሳያነቡት እንዳይቀሩ ብሎ ነበር፡፡ ታዲያ ‹እሱ መጻፉን ካልተናገረ እኛ በምን አወቅነው?› ብትሉ የዕብራውያንን መልእክት ሲጨርስ በጻፋት ‹‹ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን›› በምትለዋ የመዝጊያ ሰላምታው ነው፡፡ (ዕብ. 13፡ 25) በዚህ ሰላምታ ብቻ እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል ቢባል ደግሞ ራሱ ቅዱስ ጳውሎስ ይህቺን የምሥጢር ሰላምታ አስመልክቶ ‹‹በገዛ እጄ የተጻፈ የእኔ የጳውሎስ ሰላምታ ይህ ነው፤ የመልእክቴ ሁሉ ማስረጃ ይህ ነው፤ እንዲህ እጽፋለሁ። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።›› በማለት ተነግሮ ስለነበረ ነው፡፡ (2ተሰ. 3፡18)

ቅዱስ ሉቃስም በወንጌሉ ላይ ወንጌሉን ራሱ እንደጻፈው የሚያረጋግጡ ምልክቶችን ትቶልናል፡፡ ከእነዚህ ምልክቶች ውስጥ አንዳንዶቹ እንደ ሉቃስ በሙያቸው ሐኪም ለሆኑና በግሪክ ቋንቋ የሚነገሩ የሕክምና ሙያዊ ቃላትን የሚያውቁ ሰዎች ብቻ ሊረዷቸው የሚችሉ ሲሆኑ ሆባርት የተባለ እንግሊዛዊ ጸሐፊ ''The medical language of St. Luke'' (የቅዱስ ሉቃስ ህክምናዊ ልሳን) በሚል ርዕስ በጻፈው መጽሐፍ ላይ በሉቃስ ወንጌል ውስጥ ያሉ የሕክምና ሙያዊ ቃላትን እንደ ሂፖክራተስ ካሉ የግሪካዊያን ጸሐፍት ሥራዎች ጋር ያመሳክራል፡፡ ከቅዱስ ሉቃስ ሐኪማዊ አገላለጾች አንዳንዶቹ ደግሞ ስለ ሕክምና ብዙም እውቀት ሳይኖረንም ልንረዳቸው የምንችላቸው ናቸው፡፡

በርኩስ መንፈስ ይሰቃይ የነበረ አንድ ሰውን ታሪክ በማርቆስ ወንጌል የመጀመሪያ ምእራፍ ላይ እናነባለን፡፡ በዚያን ጊዜም በምኩራባቸው ርኵስ መንፈስ ያለው ሰው ነበረ፤ እርሱም፦ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄአለሁ፥ የእግዚአብሔር ቅዱሱ ብሎ ጮኸ። ኢየሱስም፦ ዝም በል ከእርሱም ውጣ ብሎ ገሠጸው። ርኵሱም መንፈስ አንፈራገጠውና በታላቅ ድምፅ ጮኾ ከእርሱ ወጣ።›› ይላል፡፡ (ማር.1፡25-26) ይህንኑ ታሪክ ወንጌላዊው ሉቃስ ሲጽፈው ግን እንዲህ ነበር ያለው ‹‹ኢየሱስም፦ ዝም በል ከእርሱም ውጣ ብሎ ገሠጸው። ጋኔኑም በመካከላቸው ጥሎት ሳይጐዳው ከእርሱ ወጣ።›› (ሉቃ. 4፡35) ቅዱስ ማርቆስ ጌታ ጋኔኑን ሲያወጣ ምን እንደተከሰተ ሲጽፍ ‹‹ርኩስ መንፈሱም በታላቅ ድምጽ ጮኾ ከእርሱ ወጣ›› በማለት የጋኔኑ አወጣጥ ላይ አተኩሮ ሲጽፍ ሐኪሙ ሉቃስ ግን ‹‹ጥሎት ሳይጎዳው ወጣ›› ብሎ የጋኔኑ አወጣጥና የበሽተኛው አወዳደቅ ጉዳት የሚያደርስ ስለመሆኑና ስላለመሆኑ ተጨንቆ ጻፈ፡፡ ስለ ታካሚ ደህንነት (patient safty) ማሰብ ይሏል ይኼንን ነው፡፡

የቅዱስ ጴጥሮስ አማትስ በምን እንደታመመች እናስታውስ ይሆነን? ቅዱስ ማርቆስና ቅዱስ ማቴዎስ ሕመሟን ሲገልጹ ሁለቱም ‹‹በንዳድ ታማ ነበር›› ብለዋል፡፡ (ማቴ. 8፡14 ፤ ማር. 1፡30) ሐኪሙ ሉቃስ ግን ‹‹በብርቱ ንዳድ ታማ ነበር›› በማለት በባለሙያ አገላለጽ አስቀምጦታል፡፡

ሌላው ተጠቃሽ ነገር ለሙያ አጋሮቹ ክብር ሰጥቶ ወግኖ የተናገረበት ሥፍራ ነው፡፡ አሥራ ሁለት ዓመት ደም ይፈስሳት ስለነበረችዋ ሴት ያልተሳካ ሕክምና ቅዱስ ማርቆስ ሲገልጽ ‹‹ከብዙ ባለ መድኃኒቶችም ብዙ ተሠቃየች፤ ገንዘብዋንም ሁሉ ከስራ ባሰባት እንጂ ምንም አልተጠቀመችም›› በማለት የሐኪሞቹን ድርሻ በማያሳይ አሉታዊ አገላለጽ ነበር፡፡ (ማር. 5፡25) የሐኪምን ነገር የሚውቀው ሉቃስ ግን ‹‹ትዳርዋንም ሁሉ ለባለመድኃኒቶች ከስራ ማንም ሊፈውሳት አልተቻለውም።›› በማለት ኪሳራዋ እንዳለ ሆኖ ሐኪሞቹ ግን ያላዳኗት ስላልቻሉና ከአቅማቸው በላይ ስለሆነ መሆኑንም ጨምሮ ጽፏል፡፡ (ሉቃ. 8፡43) ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ ላይ ከዚህ በተጨማሪ የሕክምናን ሒደት የሚያሳዩ ቁስል ማጠብን ፣ ዘይት ማፍሰስን ፣ በጨርቅ ማሰርን ፣ በትኩሳት ላይ ያለ ሰው ከንፈሩ እንዲርስለት የሚፈልግ ስለመሆኑ ፣ በቁስል ስለመወረስ ወዘተርፈ የሚተርኩ ምሳሌዎችን እና ታሪኮችን በጥንቃቄና ሙያዊ ቃላትን በሚያሳይ አጻጻፍ ሲያስቀምጣቸው እናገኛለን፡፡

መድኃኔዓለም ክርስቶስ በጌቴሴማኒ ሆኖ ሲጸልይ የነበረውን ጭንቀት ቅዱስ ሉቃስ ሲጽፍ ‹‹በፍርሃትም ሲጣጣር አጽንቶ ይጸልይ ነበር፤ ወዙም በምድር ላይ እንደሚወርድ እንደ ደም ነጠብጣብ ነበረ።›› ብሎ ጽፎአል፡፡ (ሉቃ. 22፡44) የጌታችንን ወዝ እንደ ደም ነጠብጣብ ስለመሆኑ ብዙ ሊቃውንት የወዙን አፈሳስና መወየብ ለመግለጽ የተቀመጠ ንጽጽር ነው እንጂ ድ አይደለም በማለት ያብራሩታል፡፡

የሕክምና ሰዎች ግን ይህን ወዝ ራሱ የደም ነጠብጣብ ነው የሚለው ሃሳብ ላይ በማዘንበል በሳይንሳዊ መንገድ ያብራራሉ፡፡ የሰው ልጅ ውስጣዊ መታወክ እና ከፍተኛ ጭንቀት ሲደርስበት ከሰውነቱ በላብ ፈንታ ደም ይወርደዋል፡፡ ይህ የደም ላብ የመከሰት እድሉ በጣም አነስተኛ ቢሆንም ለዚህ የደም ላብ የሕክምና ሰዎች የሚጠቅሱት ማሳያ ምሳሌ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ስለሁላችን በተጨነቀበት ሰዓት የወረደውን ወዝ ነው፡፡ ሐኪሞቹ ይህን ክስተት ሄማቶድሮሲስ (Hematodrosis) በማለት ይጠሩታል፡፡ ሊቁ ቅዱስ አውግስጢኖስም የሐኪሞቹን ሃሳብ የሚደግፍ ንግግርን ተናግሯል፡፡ በሊቁ ትርጓሜ ‹‹ከጌታ ሰውነት እንደ ወዝ የፈሰሰው ደም የክርስቶስ አካል ከሆነች ከቤተ ክርስቲያን የሚፈስሰው የሰማዕታት ደም ምሳሌ ነው፡፡››

ሐኪሙ ቅዱስ ሉቃስ በቀጥታ ባይጽፋቸውም በወንጌሉ ውስጥ ከሕክምና አንጻር ሊተነተኑ የሚችሉ ሌሎች መንፈሳዊ እውነታዎችንም ጽፎአል፡፡ አንዱን እንመልከትና እናብቃ፡፡ በሉቃስ ወንጌል ከተመዘገቡ የመጀመሪያ ታሪኮች አንዱ የመጥምቁ ዮሐንስ እንደ ኦሪት ሕግ በተወለደ በስምንተኛው ቀን መገረዝ ነው፡፡ (ሉቃ.1፡59) ልጅ በስምንተኛው ቀን ለምን ይገረዛል? እግዚአብሔር ይህን ቀን ለምን መረጠው? ከሳይንሱ የቀደሙት ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ግዝረት ‹ዝቅ ብሎ በሰባት ቀን ቢፈጸም ‹ልህሉህ ስለሆነ ይጎዳዋል› ሲሉ ከስምንት ቀን አልፎ ዘጠኝ ከሆነ ደግሞ ይጠነክርበታል› ብለዋል፡፡

ሳይንሳዊው ማብራሪያም ከዚህ ጋር ይስማማል፡፡ በሰውነታችን ውስጥ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ቫይታሚን ኬ እና ፕሮትሮምቢን የሚባሉ ንጥረ ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህ ንጥረ ነገሮች በሰውነታችን መኖራቸው ለደማችን መርጋት የግድ የሚያስፈልግ ነው፡፡ ሆኖም በተፈጥሮ እነዚህ ንጥረ ነገሮች መቶ በመቶ በሰውነታችን ውስጥ በበቂ መጠን ተሟልተው የሚኖሩት ከተወለድን ከስምንተኛው ቀን ጀምሮ ነው፡፡ በተለይ ፕሮትሮምቢንየተባለው ንጥረ ነገር ከመቶ ፐርሰንት በላይ ከፍ ብሎ የሚጨምርበት ብቸኛ ቀን ስምንተኛው ቀን ነው፡፡ ከዚያ ቀን በፊት ሕጻን ቢገረዝ ለአደጋ የሚጋለጥ ሲሆን ስምንተኛው ቀን ግን ቀዶ ሕክምና ያለ ስጋት ለማድረግ ሕጻኑ የሚሰማውን ሕመምም ለመቀነስ ወሳኝ ቀን ነው፡፡ ቀኑ ካለፈ ፕሮትሮምቢን ወደ መደበኛ ሥፍራው ይመለሳል፡፡ ስለ ፍጥረቱ የሚያውቀው ፈጣሪ ሳይንስና ሳይንቲስቶች ሳይኖሩ ያወጣው የኦሪት ሕግ መሆኑ ደግሞ የበለጠ ያስደንቃል፡፡

ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ዛሬ (ጥቅምት 22) ሰማዕት የሆነበት ዕለት ነው፡፡ ወደ ጻፈለትና ወደ ሣለው ጌታው ሔዶ የክብር አክሊልን ተቀዳጅቷል፡፡ ባለ መድኃኒቱ ሉቃስ ዛሬ ወደ ላይኛው ባለ መድኃኒት ፣ ራሱም መድኃኒት ወደ ሆነው ፈጣሪ ሔዷል፡፡ ጌታችን ራሱን ‹‹ባለ መድኃኒት ሆይ ትሉኛላችሁ›› ብሎ የተናገረው ባለ መድኃኒቱ ሉቃስ በጻፈው ወንጌል ላይ ብቻ ነበር፡፡ (ሉቃ.4፡23)

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ጥቅምት 2011 ዓ.ም. ተጻፈ

25/05/2022

+ ስለ ምሕረት ኪዳንህ ማረን +

እግዚአብሔር በየዘመናቱ ኪዳነ ምሕረትን (የምሕረት ኪዳንን) ገብቶ ፈጽሞአል::

እስራኤልን ከግብፅ ሲያወጣ እንዲህ ብሎ ነበር :-

"ምድራቸውን ትወርሳት ዘንድ የምትገባው ስለ ጽድቅህና ስለ ልብህ ቅንነት አይደለም፤ ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ለአባቶችህ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም የማለላቸውን ቃል ይፈጽም ዘንድ ነው" ዘዳ 9:5

እስራኤል ምድረ ርስት የገቡት በአብርሃም በይስሐቅና በያዕቆብ ኪዳነ ምሕረት (የምሕረት ኪዳን) ነበረ:: እነአብርሃም ቢሞቱም ቃልኪዳናቸው ግን ትውልድን ይታደግ ነበር::

ንጉሥ ዳዊትም ከሞተ በኁዋላ በምሕረት ኪዳኑ እስራኤልን ታድጎ ነበር::

"ስለ እኔም ስለ ባሪያዬም ስለ ዳዊት ይህችን ከተማ አድናት ዘንድ እጋርዳታለሁ" 2ኛ ነገሥ 19:34

በዳዊት ኪዳነ ምሕረት እስራኤል ከጠላቶችዋ ድና ከመቅሠፍት ተጋርዳ ነበር::

እግዚአብሔር ለቅዱሳኑ በገባው ቃልኪዳን 7 ትውልድ : 12 ትውልድ ይምራል ሲባል ይኼ እንዴት ሊሆን ይችላል? የሚል ጥያቄ መፈጠሩ አይቀርም::

እግዚአብሔር ግን የምሕረት ቃል ኪዳን ከገባ የሚዘነጋ አምላክ አይደለም::

"ምሕረቱም ለልጅ ልጅ ነው" (ሉቃ 1:50)

"ለሚወድዱኝ፥ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ እግዚአብሔር ነኝ" ይላል:: ዘጸ 20:6

የ7 እና 12 ትውልድ ሲገርመን ባለቤቱ እስከ ሺህ ትውልድ እምራለሁ ብሎን አረፈው:: መቼም አንድ ሰው በምንም ተአምር ሺህ ትውልድ ድረስ ሊወልድ አይችልም:: ቢችልም ግን እምራለሁ ይላል ጌታ::

ይህ ማለት ግን ለቀደሙት በተገባው ቃል ተማምነህ የፈለግኸውን ኃጢአት ብትሠራ ይምርሃል ማለት አይደለም:: “እነሆ ልጅ ቢወለድ ጻድቅ አባቱ የሠራውን ባይሠራ በሕይወት ይኖራልን?" ይላል ባለቤቱ:: (ሕዝ 18:11)

ሌላው ቀርቶ የመጥምቁ ዮሐንስ እና የጌታ መወለድ ሲፈጸምም የነአብርሃም ቃልኪዳን እንደ ምክንያት ተነሥቶ ነበር:: ዘካርያስ ዮሐንስን ሲያይ "ለአባታችን ለአብርሃምም የማለውን መሐላውን ቅዱሱን ኪዳን አሰበ" ብሎ ሲጸልይ ድንግሊቱም በጸሎትዋ "ለአባቶቻችን እንደተናገረ ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘላለም ምሕረቱ ትዝ እያለው እስራኤል ብላቴናውን ረድቶአል" ብላ ለአብርሃም ቤት በገባው ቃል ኪዳን ከአብርሃም ዘር መወለዱን አስታውሳለች:: (ሉቃ 1:55:72)

እግዚአብሔር ለቅዱሳን በገባው ቃል ብቻ ሳይሆን ስለ ስሙም ይምረናል::

እስራኤልን በዳዊት ቃልኪዳን ሲምር እንዲህ አለ:-
"ስለ እኔም ስለ ባሪያዬም ስለዳዊት ከተማይቱን እምራለሁ" 2ኛ ነገሥ 19:34

ስለ ስምህ ማረን ብለን ስለ ቅዱሳንህ ማረን የምንለው ራሱ እግዚአብሔር ሲናገር ያየነውን ይዘን ነው:: ኪዳናችን "በእንቲአከ ወበእንተ ፍቁር ወልድከ እግዚእነ ኢየሱስ" (ስለራስህና ስለተወደደ ልጅህ ጌታችን ኢየሱስ) ቅዳሴያችን "በእንተ ስምከ አጽንዓነ" (ስለ ስምህ ብለህ አጽናን) የሚለው በስሙ እንድንለምን የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለሆነ ነው::

ስለ ዳዊት ስለ አብርሃም ስለ ድንግል ማርያም ብለህ ማረን ማለት ከመጽሐፍ ቅዱስ የተገኘ የጸሎት ዘይቤ መሆኑ ለማይዋጥለት ሰው መጽሐፍ ቅዱስ አልፎ ተርፎ "ስለ ሰይጣን ብለህም" ይላል::
"ከሕፃናትና ከሚጠቡ አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ
ስለ ጠላትህ" ይላል:: (መዝ 8:2) ጠላት ዲያቢሎስ ይፈር ብለህ የሕፃናትን አፍ በምስጋና ሞላህ ሲል ነው:: ርኩስ ዲያቢሎስ ደስ አይበለው ብሎ እግዚአብሔር የሚሠራ ከሆነ መላእክት ደስ ይበላቸው ብለህ "በእንተ ሚካኤል በእንተ መላእክት መሐረነ ክርስቶስ" ብንል ምንኛ ይሰማን ይሆን?

የወላዲተ አምላክ ኪዳነ ምሕረት (የምሕረት ኪዳን) ከአብርሃም ከዳዊት ቃል ኪዳን ይበልጣል:: እግዚአብሔርን በቤቱ ካስተናገደው አብርሃም ይልቅ ለእግዚአብሔር ቤቱ የሆነች ድንግል አትበልጥምን? በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ከዘለለው ዳዊት ይልቅ ለእግዚአብሔር ታቦት የሆነችው ድንግል አትበልጥምን? ስለዚህ የእርስዋ ቃልኪዳን ከሁሉ ይበልጣል::

እርስዋ ምሕረት ለማሠጠት የምታስታውሰው የተገባላትን ኪዳን ብቻ አይደለም:: በብርድ ወራት በጨርቅ የጠቀለለችውን : ድንግልናዊ ወተትዋን ያጠባችውን : በስደት ይዛው የተንከራተተችውን : በፊቱ ላይ የወረደውን ዕንባዋን እያስታወሰች እንድትለምንልን በቅዳሴያችን የምንማጸናት ለዚህ ነው::

የምሕረት ቃል ኪዳን ግን የሚሠራው እኛ በቃልኪዳኑ ስናምንና ምሕረት ለማግኘት ስንፈልግ አቅማችን በቻለው ጥቂትም አስተዋጽኦ ሲኖረን ነው::

ያ የመቶ አለቃ ወደ ጌታ መጥቶ ባሪያዬን ፈውስልኝ ሲለው የአይሁድ ሽማግሌዎች እንዲህ ብለው ጌታችንን ተማጽነውት ነበር :-

"ይህን ልታደርግለት ይገባዋል ሕዝባችንን ይወዳልና ምኵራብም ራሱ ሠርቶልናል፡ ብለው አጽንተው ለመኑት" (ሉቃ 7:5)

የአይሁድ ሽማግሌዎች እንዲህ ካሉ አንድ ጻድቅ "ድሆችን ይወዳል ቤተ መቅደስም አሳንፆአልና ማረው" ብሎ ቢለምን ምን ይደንቃል?

የኤልያስ ልመና ደግሞ ይደንቃል:: ስድስት ወር ሙሉ የመገበችው የሰራፕታዋ መበለት ልጅ (የኁዋላው ነቢዩ ዮናስ) ድንገት ሲሞትባት እንዲህ ብሎ ጸለየ :-

"ወደ እግዚአብሔርም፦ አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ ልጅዋን በመግደልህ ይህችን ትቀልበኝ የነበረቺቱን ባልቴት እንዲህ ደግሞ አስጨነቅኻትን? ብሎ ጮኸ" 1 ነገሥ 17:20 ጻድቃን ያገለገሉአቸው ሰዎች ሲጎዱ እንዲህ በምልጃ ይጮኻሉ::

ሆኖም በቃልኪዳን ለመጠቀም እንደ ሰራፕታዋ መበለት ትንሽ ዱቄት ትንሽ መልካምነት ያስፈልጋል:: እግዚአብሔር ትንሹን በቸርነቱ ያበዛዋል:: ጥርኝ ዱቄት ጥርኝ ደግነት ጥርኝ ውኃ ከእኛ ይጠበቃል::

ጥርኝ (Civettictis civetta) በኢትዮጵያ ብቻ የምትገኝ አጥቢ እንስሳ ናት:: ለየት የሚያደርጋት ከሰውነትዋ የሚመነጭና በዛፍ ላይ የምትቀባው ዝባድ ተብሎ የሚጠራ ቅባት ነው:: ይህንን በጣም ትንሽ ቅባት ጥርኝ በዛፍ ላይ ከተወችው በኁዋላ እየቆየ ቀለሙከቢጫ ወደ ቡኒ ይቀየራል:: ሽታውም እስከ አራት ወር ይቆያል:: ይህንን ቅባት ሴቬቶን ወደሚባል ውሕድ አጣርተው ውድ የሆነ ሽቶ የሚሠሩ ፋብሪካዎች ይጠቀሙበታል:: ጥርኝ በዛፍ ላይ የተወችው ጥቂት ቅባት ሽታው ዓለምን ያዳርሳል:: እግዚአብሔርም እንዲህ ነው ምሕረትን ለማድረግ ጥቂት ነገር ይፈልጋል:: እንደ በላኤ ሰብእ ጥርኝ ውኃ ሲያገኝ ከድንግሊቱ ኪዳነ ምሕረት ጋር ደምሮ ይምርሃል:: እንደ ሕዝቅያስ ጥርኝ ዕንባ ሲያገኝ ከዳዊት ቃልኪዳን ጋር ደምሮ ይምራል:: እንደ ሙሴ አታጥፋቸው የሚል ጥርኝ ምልጃ ሲያገኝ ከአብርሃም ቃልኪዳን ጋር ደምሮ ይምራል::

ጥርኝ ውኃ : ጥርኝ ዕንባ : ጥርኝ ደግነት ብቻ አንዳች ጥርኝ መልካምነት ከእኛ ይፈልጋል::

"በብዙ ወይም በጥቂት ማዳን እግዚአብሔርን አያስቸግረውምና" 1ኛ ሳሙ 14:6

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
የካቲት ኪዳነ ምሕረት
2013 ዓ.ም

15/05/2022

+ የዘኬዎስ ዛፍ +

ዘኬዎስ ቁመቱ አጭር ዝናው ግን ረዥም የሆነ ሰው ነው፡፡ ይህንን ሰው የምናውቀው በኢያሪኮ መንገድ የሚያልፈውን ክርስቶስ ለማየት በአንዲት የሾላ ዛፍ ላይ ወጥቶ ነው፡፡ ወደዚያች ዛፍ የወጣው ቁመቱ አጭር በመሆኑና በሕዝቡ መብዛት ምክንያት ክርስቶስን ሊያየው ባለመቻሉ ነው፡፡ መቼም ሰው በበዛበት ፣ ግርግርና በሆይ ሆይታ በሞላበት ቦታ ክርስቶስን ማየትም ሆነ ከአምላክ ጋር መነጋገር ለአጭርም ለረዥምም ሰው ከባድ ነው፡፡ እያንዳንዳችን ጌታን ለማየት ከጫጫታና ግርግር ተለይተን የምንወጣበት የየራሳችን ሾላ የሚያስፈልገንም ለዚህ ነው፡፡

ዘኬዎስ በሙያውም ከአመንዝሮችና ከወንጀለኞች ጋር የተቆጠረ ቀራጭ ነበር፡፡ በሰው ፊት ደፍሮ ‘ጌታን ማየት እፈልጋለሁ’ እንዳይል ፣ ከእርሱ ቀድሞ ዓይኑ እንደበራለት በርጤሜዎስ ‘የዳዊት ልጅ ሆይ ማረኝ’ ብሎ በሕዝብ ፊት እንዳይጮህ ‘አንተን ብሎ ጸሎተኛ! ትንሽ አታፍርም?’ የሚያሰኝ ሕይወት ስለነበረው ጌታን በሩቅ ማየት ብቻ ይበቃኛል ብሎ ከዛፍ ላይ ወጣ፡፡

ዘኬዎስ ወደ ዛፍ የወጣው ጌታን ለማየት እንጂ ለመታየት አልነበረም፡፡ የእርሱ ፍላጎት ከሰው መሃል ገብቶ ሳይከለል ጌታውን ማየት ነበር:: መታየት ከሚሹ ይልቅ እርሱን ማየት የሚሹትን ለይቶ የሚያውቀው ክርስቶስ ይህንን ቀራጭ ከሕዝቡ ለይቶ ተመለከተው፡፡

ጌታ ሲያየው ሕዝቡ ሁሉ ዓይኑን ወደሱ መለሰ:: በመድኃኔዓለም የምሕረት ዓይን ከታየህ በእርግጥም ዓለም ሁሉ ያይሃል፡፡ ክርስቶስ ስላየው ሁላችንም ዘኬዎስን አየነው ፣ ታሪኩም በምንሳለመው ቅዱስ ወንጌል ላይ ተጻፈ፡፡

ጌታ በዓይኖቹ ይመልከትህ እንጂ ምንም ክፉ ብትሆን የሕይወት ታሪክህ ወንጌል ይሆናል፡፡ አንተ እርሱን የሚሻ ልብ ካለህ ድምጽ አውጥተህ ባትጠራውም ፣ ጸሎት ማሳመር ባትችልም የልብህን ጩኸት ሰምቶ ይጠራሃል፡፡ ለዘኬዎስ የሆነለት ይህ ነበር፡፡ እንደ አጋር ‘የሚያየኝን አየሁት’ ብሎ ሊዘምር የሚችል የሐዲስ ኪዳን ሰው እርሱ ሆነ፡፡ ጌታን ሊያይ ከዛፍ ወጥቶ በጌታው ታይቶ ወረደ፡፡ ወደ ቤታችን ለመግባት ጋባዥ የማይፈልገው ክርስቶስ የዘኬዎስን ልብ አይቶ ዛሬ በአንተ ቤት እሆናለሁ አለው፡፡

የቀራጮች መሰብሰቢያ የሆነችው የዘኬዎስ ቤት የጌታና የደቀ መዛሙርቱ ማረፊያ ቤት ሆነች፡፡ የግፍ ገንዘብ ማከማቻ የነበረችው የክፉዎች አዳራሽ የሰማያዊው እንግዳ የክርስቶስ ቤተ መቅደስ ሆነች፡፡ ሕሙማን ሊፈወሱ ከዚያች ቤት ዙሪያ ሰፈሩባት፡፡ ሐኪሙ ጌታ ገብቶባታልና የዘኬዎስ ቤት ሐኪም ቤት ሆነች::

በዚህ ደስ ያለው ዘኬዎስም ‘ካለኝ እኩሌታውን ለድሆች እሰጣለሁ ፤ በሐሰት የከሰስሁትን አራት እጥፍ እክሳለሁ’’ አለ፡፡ የሕይወት ለውጥ ከሌለ ደግሶ ማብላት ብቻውን ጽድቅ እንደማይሆነው አውቆ አለመታዘዙን በመታዘዝ ፣ ስርቆቱን በምጽዋት ሊበቀል ተነሣ፡፡ የመዳን ቀንድ ክርስቶስም ‘’ለዚህ ቤት መዳን ሆኖለታል’ አለው፡፡

የዘኬዎስ ታሪክ ብዙ ምሥጢር ብዙ ምክር የሚወጣው ነውና ለዛሬ አንዱን ሰበዝ ብቻ እንምዘዝ ፤

እንደሚታወቀው የዘኬዎስ ከዚያ በኋላ ያለው ታሪኩ አልተጻፈም፡፡ ከሱ ታሪክ ጋር የተያያዘችዋ ቅርስ እርሱ የወጣባትና ጌታውን ያየባት የሾላ ዛፍ ነበረች፡፡ በኢያሪኮ መንደር የምትገኘው ይህች ዛፍ ለሌሎች ሰዎች ተራ ዛፍ ብትሆንም ለዘኬዎስ ግን ‘‘የሕይወት ዛፍ’’ ናት፡፡ ምናልባትም ዘኬዎስ ከመስቀል በፊት ጌታን ያየባት የከበረች ዕፅ ይህች ዛፍ ናት፡፡ ጌታው እርሱን ብሎ ሳይሰቀል በፊት እሱ ጌታን ብሎ የተሰቀለባትና መድኃኒቱን ያየባት ይህች ዛፍ ለዘኬዎስ ትልቅ ባለውለታው ናት፡፡

ዘኬዎስ ይህችን ዛፍ ባየ ቁጥር ምን ይሰማው ይሆን? ምንም እንኳን ትልቅ ዛፍ ብትሆንም እርሱ ግን እንደ ችግኝ በስስት ዓይን ሳይመለከታት የሚቀር አይመስላችሁም? ባለፈ ባገደመ ቁጥር በፍቅር የሚስማት ፣ ጌታውን ሲያስብ ለጸሎት የሚመጣባት : ቅጠሎችዋን በፍቅር እየነካካ ዙሪያዋን የሚያጸዳላት ጌታን ያየባት ክብርት ዛፉ ናት፡፡

አይበለውና ይህች ዛፍ ትቆረጥ ቢባል ዘኬዎስ ምን የሚል ይመስላችኋል? በእጆቹ ግንድዋን ታቅፎ "አንኩብኝ!" አይል ይሆን? ለማገዶ ትዋል ተብሎ ቢወሰንባትስ? እሳት ቢነድባትስ? የዘኬዎስ ልብ ምን ያህል ይቆስል ይሆን? ጌታውን ያየባት መሰላሉ ሕይወቱ የተለውጠባት የመድኃኒት ዛፍ ተቆርጣ ተማግዳ ቢያይ ዘኬዎስ ልቡ በኀዘን ይደማል::

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስትቃጠል ፣ ስዘረፍ ፣ ስትደፈር የሚሰማንም ይህ ነው! በኃጢአት ቁመታችን አጥሮ ፈጣሪን ማየት ሲሳነን በእርስዋ ላይ ወጥተን ጌታን ያየንባት ፣ የታሪካችን መስመር ተቀይሮ ለየቤታችን መዳንን ያገኘንባት ፣ ብዙ ዘኬዎሶችን ተሸክማ ከጌታ ያገናኘች እውነተኛዋ ዛፍ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡
እርስዋን የሚነኩ ሁሉ የመውጊያውን ብረት ይቃወማሉ ፤ ‘አይነኩ ከነኩ ያድሯል ሲታወኩ’ የተባለላት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ይህ ዘመን ስለዚህች የሕይወት ዛፍ ፣ የሰማይ ደጅ የምተጋበት ፣ ጌታን ያየንባትን ዛፍ ከበብን ከመቼውም ጊዜ በላይ በየመክሊታችን የምሠራበት ፣ ችግርዋን መፍታት ቢያቅተን ችግር ላለመሆን የምጥርበት ጊዜ ነው፡፡

ስለዚህች የኃጥአን ተስፋ ስለሆነችው የዘኬዎስ ዛፍ ገጣሚ ዳዊት ግርማ የአባ ጳውሊ ራእይ በተባለ የግጥም መድበል ላይ (paraphrased version) እንዲህ ብሎላታል ፦
ቤተ ክርስቲያን ደብረ ብዙኃን
ምነው እንደ ዳዊት ዘመን
ዛሬም በሆንሽ በድንኳን
ምቀኛ ሲገፋሽ ጠቅልዬሽ እንድሸሽ
ምቀኛ ሲተውሽ መልሼ እንድተክልሽ

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
አዲስ አበባ
ጥር 3 2012
ፎቶ :- ጸሐፊው ከዘኬዎስ ዛፍ አጠገብ

07/04/2022

አመንዝራ 😁

Address

Awassa

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Belay tiguh posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Contact The Business

Send a message to Belay tiguh:

Share