28/03/2026
23ኛው ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድር እና 19ኛው የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል ከነገ ጀምሮ በሐረሪ ክልል መካሄድ ይጀምራል
23ኛው ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድር እና 19ኛው የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል ከነገ ጀምሮ በሐረሪ ክልል እንደሚካሄድ የክልሉ ስፖርት ኮምሽን አስታወቀ።
የክልሉ ስፖርት ኮምሽን ኮምሽነር ሙራድ አብዲ ውድድሩንና ፌስቲቫሉን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ 23ኛው ሀገር አቀፍ የባህል ስፖርት ውድድርና 19ኛው የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫሉን በድምቀት ለማክበር የክልሉ መንግስት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል።
በዚህም የተለያዩ ኮሚቴዎችና ግብረ ሃይል ተቋቁሞ የተለያዩ ተግባራትን ሲከናወኑ መቆየቱን ጠቅሰው በክልሉ ለሚካሄደው የባህል ስፖርቶች ውድድር እና ፌስቲቫል ዝግጅት መጠናቀቁን አመልክተዋል።
መርሃ ግብሩም የኢትዮጵያን ህብረ ብሄራዊ አንድነት፣ ብዝሃነት እና አብሮነት የሚተዋወቅበት መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ ሐረር ያላትን አኩሪና ማራኪ ባህላዊ እሴቶችን፣ የመስህብ ስፍራዎችንና በኮሪደር ልማት የተከናወኑ ስፍራዎችን በማስጎብኘት የቱሪዝም ዘርፉን የማጎልበት ስራ ይከናወናል ብለዋል።
በውድድሩና ፌስቲቫሉ ላይ ከአፍሪካ ባህል ስፖርቶች እና ጨዋታዎች ኮንፌዴሬሽን የተጋበዙ የክብር እንግዶች እንደሚታደሙበትም ጠቁመዋል።
በነገው እለት በከተማው በሚገኘው ኢማም አህመድ ስታድየም ጅማሮውን የሚያደርገው የባህል ስፖርቶች ውድድር እና ፌስቲቫል ከ1500 በላይ ስፖርተኞች በ11 የስፖርት አይነት እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።
ለአንድ ሳምንት የሚቆየው የባህል ስፖርቶች ውድድር እና ፌስቲቫል "የባህል ስፖርቶች ልማት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚካሄድ ከመርሃ ግብሩ ለማወቅ ተችሏል።