23/08/2026
ጌታ ሆይ፣ ዘመኔን ቀይር
ጌታ ሆይ፣ ምንም የተቀየረ ነገር አላይም፤ የሚቀየርም አይመስለኝም። ሁሉም ነገር ከምችለው በላይ እየሆነብኝ ነው።
ጌታ ሆይ፣ ምን ማድረግ እንዳለብኝ አንተ ታውቃለህ። እኔ የማላውቀውን አንተ ታውቃለህ፤ የማልችለውንም አንተ ትችላለህ። እባክህ እርዳኝ፣ አግዘኝ።
እኔ በደለኛና ኃጢአተኛ ሰው ነኝ፤ ነገር ግን ምሕረትህ ከኃጢአቴ ይበልጣል። አባቶይ፣ ብርታቱን አንተ ስጠኝ። የእውነት ልቤ ደክሞኛል፤ ተስፋ መቁረጥ እየበዛብኝ ነው።
ሲነጋም ያው ነው፤ ሲመሽም ያው ነው። መከፋት፣ ማዘን፣ መተከዝና መጨነቅ የዕለት ተዕለት ሕይወቴ ሆኗል።
ጌታ ሆይ፣ እኔ የማልችለውን አንተ አድርግልኝ። የተዘጋውን በር ክፈትልኝ፤ የጠፋውን ተስፋ መልስልኝ፤ የደከመውን ልቤን አበርታልኝ።
ጌታ ሆይ፣ ዘመኔን ቀይር። ሕይወቴን ቀይር። የልጆቼን እንባ ወደ ደስታ ቀይር። የቤተሰቤን ጭንቀት ወደ ሰላም ቀይር። የዛሬውን መከራ የነገ ምስክርነት አድርገው።
ሁሉን የምትችል ጌታ አንተ ነህ። ሰው የሚያየው መከራዬን ነው፤ አንተ ግን የልቤን ታውቃለህ።
እባክህ አትተወኝ። እጄን ያዝ። ከዚህ ጨለማ አውጣኝ። እንደገና ተስፋ እንዳደርግ፣ እንደገና እንድስቅ፣ እንደገና እንድኖር ኃይል ስጠኝ።
ጌታ ሆይ፣ አንተ አግዘኝ። አንተ አድነኝ። አንተ ዘመኔን ቀይር። አሜን።